ሀሁ ቡክስ

- የሀሁ ቡክስ ዋና ዐላማ ጥራት ያላቸው ተረቶች እና ታሪኮችን፣ ጨዋታዎችን እና መዝሙሮችን፣ እንዲሁም ሌሎች ትምህርታዊ ቁሳቁስን ለልጆች በዐማርኛ ቋንቋ ማሳተም ነው።

- ለጐልማሶች ተስማሚ የኾኑ የዐማርኛ ቋንቋ መማሪያ ቁሳቁስ ማሳተምም የሀሁ ቡክስ ተጨማሪ ዐላማ ነው።ዐዲስ የሀሁ ቡክስ ኅትመት


እኒህን ዐላማዎቹን የሚያግዝ፣ ከነርሱም ጐን ዐብሮ የሚራመድ የቤተሰብ መጽሔትን ሀሁ ቡክስ ያሳትም ነበር። መጽሔቱን - ቡቃያ - በመጀመሪያ እና ኹለተኛ ቅጾች በተጠቃለሉ 16 ዕትሞች ለንባብ አብቅቷል እኒህ ዕትሞች ተሽጠው በማለቃቸው የሌሎች ፈላጊዎችን ጥያቄ ለማሟላት አልቻልንም። ስለዚህ እኒህን ዕትሞች በአንድ ጥራዝ ሰብስቦ ለማሳተም ዝግጅት በማድረግ ላይ ነው። በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ የምንወድደው ነገር አለ፤ ልጆችን ዐማርኛ የሚያስተምሩ አንዳንድ የማኅበረሰብ ማእከሎች (community centres) የቡቃያ ዕትሞችን በማስተማሪያ ቁሳቁስ መልክ ተጠቀምውባቸው ነበር። በመጽሐፍ መልክ የሚወጣው የቡቃያ ዕትሞች መድበል ይህን ጠቀሜታቸውን ለደንበኞች እንደሚያቀርብ ተስፋ እናደርጋለን።

በመጻሕፍት ኅትመት ረገድ ሀሁ ቡክስ ዐዲስ ባለ ክልዔ ልሳን (bilingual) የልጆች መጽሐፍ አሳትሟል። መጽሐፉ - ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ-ነገሥት ዘኢትዮጵያ - በኅሪት በላይ የተደረሰ ታሪካዊ ልብ-ወለድ ሲኾን 8-15 ዕድሜ ክልል ያሉ ልጆችን የሚያማልል ነው። ኢትዮጵያ አንድነቷን መልሳ በዘመናዊ ጐዳና እንድትጓዝ መሠረት የጣሉትን ዐፄ ቴዎድሮስ ከልጆች ጋር ያስተዋውቃል። በዐማርኛ እና እንግሊዝኛ መታተሙም ለቋንቋ ተማሪዎች ትልቅ ርባና አለው። የመጽሐፉን ቅጂ ለመግዛት መረጃ እና ማዘዣ ያገኙ ዘንድ ይህን ይጫኑ።

ሀሁ ቡክስ በዚህ ድር-ቀዬው (website)አማካይነት በኢንተርኔት ለሚጠቀሙ ኹሉ ጥራት ያላቸውን የልጆች መጻሕፍት ምን ላንብብ በተሰኘ ድር-ገጽ (webpage) መገምገም ጀምሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደራሲያን ለ/ስለ ኢትዮጵያውያን ልጆች የሚያሳትሟቸው መጻሕፍት ቍጥር እያደገ ነው። ግን ይህ ደስ የሚያሰኝ ዐዲስ እድገት በልጆች እና ወላጆች፣ አስዳጊዎች እና መምህራን ዘንድ ገና የታወቀ አይመስልም። ስለዚህ የግምገማ ገጹ አንድ ዐላማ በቅርቡ በዐማርኛ እና/ወይም በእንግሊዝኛ ስለታተሙ መጻሕፍት ይዘት፣ አቀራረብ፣ ሽያጭ፣ ወዘተ. መረጃ በማቅረብ ጕዳዩ የሚመለከታቸውን ክፍሎች ግንዛቤ ከፍ ማድረግ ነው።

በዐማርኛ ከቀረቡት ግምገማዎች ጥቂቶቹ ከኹለተኛው ቅጽ የቡቃያ ዕትሞች የተቀዱ ናቸው። እነርሱን እና ሌሎች ዳሰሳዎችን ይህ ድር-ቀዬ ያስተናግዳል። ዳሰሳዎቹ ከሞላ ጐደል በእንግሊዝኛ እንዲቀርቡ ጥረት ያደርጋል። ይህም ሀሁ ቡክስ ካሉት ዐላማዎች አንዱን - ለልጆች ተስማሚ የኾኑ ዐዳዲስ ኅትመቶችን ለአንባቢያን የማስተዋወቅ ዐላማውን - ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል የሚል እምነት አለን።

በዚህ ረገድ ደራሲያን ያሳተሟቸውን የልጆች መጻሕፍት ቅጂዎች ቢልኩልን ምን ላንብብ ገጻችን ላይ ዳሰሳ በማቅረብ ልናስተዋውቅላቸው እንችላለን።

በተጨማሪ የእንግሊዝኛውን ገጽ ይመልከቱ